ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 47

1 ፤ ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር።
2 ፤ በሰሜኑም በር በኩል አወጣኝ፤ በስተ ውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በስተ ውጭ ወዳለው በር አዞረኝ፤ እነሆም፥ ውኃው በቀኙ ወገን ይፈስስ ነበር።
3 ፤ ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ።
4 ፤ ደግሞ አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ጕልበት ደረሰ። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ።
5 ፤ ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ።
6 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? አለኝ። አመጣኝም፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ።
7 ፤ በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ።
8 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል።
9 ፤ ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ወንዙ በመጣበት ስፍራ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ይህም ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ የባሕሩም ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል።
10 ፤ አጥማጆችም በዚያ ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ ጀምሮ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣዎች በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ።
11 ፤ እረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን ጨው እንደ ሆነ ይኖራል እንጂ አይፈወስም።
12 ፤ በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ርስት አድርጋችሁ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት እድል ፈንታ ይሆናል።
14 ፤ ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ ምዬ ነበርና እናንተ እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት ይህችም ምድር ርስት ትሆናችኋለች።
15 ፤ የምድሪቱም ድንበር ይህ ነው። በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጽዳድ መግቢያ፤
16 ፤ ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን።
17 ፤ ድንበሩ ከባሕሩ በደማስቆ ድንበር ላይ ያለው ሐጸርዔናን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። የሰሜኑ ድንበር ይህ ነው።
18 ፤ የምሥራቁም ድንበር በሐውራን በደማስቆና በገለዓድ በእስራኤልም ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ የምሥራቁ ድንበር ይህ ነው።
19 ፤ የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። የደቡቡ ድንበር ይህ ነው።
20 ፤ የምዕራቡም ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። የምዕራቡ ድንበር ይህ ነው።
21 ፤ እንዲሁ ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ለእናንተ ትካፈላላችሁ።
22 ፤ ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ።
23 ፤ መጻተኛውም በማናቸውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ በዚያ ርስቱን ትሰጡታላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።