መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 30

1 ፤ አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ።
2 ፤ ሙሉ ሰው መሆናቸው ጠፍቶባቸው ነበርናየእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል?
3 ፤ በራብና በቀጠና የመነመኑ ናቸው፤የመፍረስና የመፈታት ጨለማ ወዳለበትወደ ምድረ በዳ ይሸሻሉ።
4 ፤ በቍጥቋጦ አጠገብ ያለውንጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ፤የክትክታ ሥር ደግሞ መብላቸው ነው።
5 ፤ ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፤በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል።
6 ፤ በሸለቆ ፈረፈርና በምድር ጕድጓድበድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ።
7 ፤ በቍጥቋጦ መካከል ይጮኻሉ፤ከሳማ በታች ተሰብስበዋል።
8 ፤ የሰነፎችና የነውረኞች ልጆች ናቸው፤ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው።
9 ፤ አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው።
10 ፤ ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም።
11 ፤ የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፤እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል።
12 ፤ በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥እግሬንም ይገለብጣሉ፤የጥፋታቸውን መንገድ በእኔ ላይ ይጐድባሉ።
13 ፤ ጐዳናዬን ያበላሻሉ፤ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ።
14 ፤ በሰፊ ፍራሽ እንደሚመጡ ይመጡብኛል፤በባድማ ውስጥ ይንከባለሉብኛል።
15 ፤ ድንጋጤ በላዬ ተመለሰችብኝ፥ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱአታል፤ደኅንነቴም እንደ ደመና አልፋለች።
16 ፤ አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤የመከራም ዘመን ያዘችኝ።
17 ፤ በሌሊት አጥንቴ በደዌ ተነደለች፥ጅማቶቼም አያርፉም።
18 ፤ ከታላቁ ደዌ ኃይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤እንደ ቀሚስ ክሳድ አነቀችኝ።
19 ፤ እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥አፈርና አመድም መሰልሁ።
20 ፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም።
21 ፤ ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤በእጅህም ብረታት አስጨነቅኸኝ።
22 ፤ በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስቀመጥኸኝ፤በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ።
23 ፤ ለሞት ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና።
24 ፤ ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጁን አይዘረጋምን?በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን?
25 ፤ ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን?ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን?
26 ፤ ነገር ግን በጎነትን በተጠባበቅሁ ጊዜ ክፉ ነገር መጣችብኝ፤ብርሃንን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ ጨለማም መጣ።
27 ፤ አንጀቴ ፈላች፥ አላረፈችም፤የመከራም ዘመን መጣችብኝ።
28 ፤ ያለ ፀሐይ በትካዜ ሄድሁ፤በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ።
29 ፤ ለቀበሮ ወንድም፥ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ።
30 ፤ ቁርበቴ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፤አጥንቴም ከትኵሳት የተነሣ ተቃጠለች።
31 ፤ ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ ቃል ሆነ።