መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 23

1 ፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ዛሬም ደግሞ የኅዘን እንጕርጕሮዬ ገና መራራ ነው፤እጁ በልቅሶ ጩኸቴ ላይ ከብዳለች።
3 ፤ እርሱን ወዴት እንዳገኘው ምነው ባወቅሁ!ወደ ተቀመጠበትስ ስፍራ ምነው በደረስሁ!
4 ፤ በፊቱ ሙግቴን አዘጋጅ ነበር፥አፌንም በማስረጃ እሞላው ነበር።
5 ፤ የሚመልስልኝም ቃል ምን እንደ ሆነ አውቅ ነበር፥የሚለኝንም አስተውል ነበር።
6 ፤ በኃይሉ ብዛት ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን?እንኳን! ያደምጠኝ ነበር።
7 ፤ ቅን ሰው ከእርሱ ጋር በዚያ ይከራከር ነበር፤እኔም ከፈራጄ ለዘላለም እድን ነበር።
8 ፤ እነሆ፥ ወደ ፊት እሄዳለሁ፥ እርሱም የለም፤ወደ ኋላም እሄዳለሁ፥ እኔም አላስተውለውም፤
9 ፤ ወደሚሠራበት ወደ ግራ ብሄድ አልመለከተውም፤በቀኜም ይሰወራል፥ አላየውምም፤
10 ፤ የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ።
11 ፤ እግሬ ወደ እርምጃው ተጣብቆአል፤መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ፈቀቅም አላልሁም።
12 ፤ ከከንፈሩ ትእዛዝ አልተመለስሁም፤የአፉን ቃል በልቤ ሰውሬአለሁ።
13 ፤ እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው?ነፍሱም የወደደችውን ያደርጋል።
14 ፤ በእኔ ላይ የተወሰነውን ይፈጽማል፤እንደዚህም ያለ ብዙ ነገር በእርሱ ዘንድ አለ።
15 ፤ ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፤ባሰብሁም ጊዜ ከእርሱ ፈራሁ።
16 ፤ እግዚአብሔር ልቤን አባብቶታልና፥ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል።
17 ፤ ከጨለማው የተነሣ፥ድቅድቁም ጨለማ ፊቴን ከመክደኑ የተነሣ አልደነገጥሁም።